
አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 የዘመናት የትግል ውጤት ነው - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 በዓል በሆሳዕና ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በአሉን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 የዘመናት የትግል ውጤት ነው ብለዋል። ስለ ሴቶች ስናነሳ ስለ ህብረተሰብ፣ ስለ ሀገር ግንባታ፣ ስለ ትውልድ ቀጣይነት እና ትውልድን ስለ ማጽናት መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል። በመደመር መንገድ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የምናደርገው ጉዞ መሳካት የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል!" በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን በዓል እውቅና መስጠት ተገቢ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። ሴቶች የታገሉት ለእኩልነት ብቻ ሳይሆን ለፍትህ፣ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ለሀገር ግንባታ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል። የካራ ማራን የድል በዓል በተከበረበት ማግስት ማርች 8 መከበሩ የተለየ ያደርገዋል ሲሉም ጠቁመዋል። በዘመናዊ መሳሪያ እራሱን ያደራጀው የጣሊያን ሰራዊት ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ በተገኘው ድል የእናቶች ሚና ከፍተኛ እንደነበርም አስታውሰዋል። ይህ አመት ለኢትዮጵያ የከፍታ ዓመት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የተጀመረው የለውጥ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። በኢፌዲሪ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አይሻ የህያ በበኩላቸው ሴቶች በጾታ ምክንያት የሚደርስባቸውን መድሎ እና በደል በመታገል ያደረጉትን ጉልህ አስተዋጽኦ ለመዘከር በዓሉ ሲከበር ቆይቷል። ሴቶች በኢኮኖሚ በዲፕሎማሲ፣በሀገር መሪነት ፣በግጭት አፈታት በሰላም ግንባታ እና በሌሎችም መስኮች ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሴቶች ለስርዓተ ጾታ እኩልነት እና ለመብት ትግል ማድረጋቸውን በአብነት ጠቅሰዋል። ሴቶችን በኢኮኖሚ ፣በማህበራዊ እና በውሳኔ ሰጪነት ከማብቃት አንጻር በርካታ ተግባራትን ማከናወን መቻሉት አብራርተዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሐመድ ናስር እንደገለጹት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 በዓል ሲከበር የሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አብይ አጀንዳ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። የክልሉ መንግስት ለሴቶች ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው ብለዋል። የሴቶች የልማት ህብረት ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል ፣ የተጠቃሚነታቸው ጉዳይ በተጨባጭ እንዲረጋገጥ እንዲሁም በቅንጅት የመስራት በጥበብ እና በዲሲፕሊን እንዲመራ ጥረት ተደርጓል ብለዋል። በክልሉ 1ሚሊየን 163ሺ 185 ሴቶችን በ39ሺ 464 ልማት ህብረት በማደራጀት የግንዛቤና የንቅናቄ ስራዎች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ኃላፊዋ አብራርተዋል። በክልሉበመሬት ባለቤትነት፣በመስኖ ልማት ስራ፣ በሌማት ትሩፋት፣በእንስሳት እርባታ ስራዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ወ/ሮ ዘቢባ መሐመድ ናስር ጠቁመዋል። ይህን ተከትሎም በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በመሳተፋቸው 398 ሚሊየን443ሺ 487 ብር መቆጠባቸውን ኃላፊዋ በአብነት ጠቅሰዋል።