
ሴቶችን በስልጠና በማብቃት የመሪነት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ ለሴት አመራሮችና ፈፃሚዎች በሳጃ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የስልጠና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልባር ኡስማን፣ ሴቶችን በስልጠና በማብቃት የመሪነት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሴቶችን ማብቃት ሰፊውን ማህበረሰብ ማገልገል በመሆኑ በሁሉም ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ሴቶችን ማፍራት ላይ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚኖራቸው አበርክቶ አንፃር በመሪነት ያላቸው ተሳትፎ በቂ አለመሆኑን ያነሱት አቶ አብዱልባር፣ ስረዓተ ፆታን በእያንዳንዱ ተግባር አካቶ በመተግበር የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ተናግረዋል። በተግባር አፈፃፀም ግንባር ቀደም ሴት አመራሮችና ፈፃሚዎችን ማፍራት ላይ ያተኮረ ስልጠና ስለመሰጠቱ ያስታወሱት የዘርፍ ኃላፊው፣ የስልጠናውን አፈፃፀም አስመልክቶ ከባድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቀጣይ ውጤታማነቱ ላይ ክትትል እንደሚደረግም ጠቁመዋል። የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትልና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ነጅሚያ ራህመቶ በክልሉ የተጀመሩ የልማት ተግባራትን ለማሳካት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሴቶች በልማት ተግባራት የሚኖራቸው አበርክቶ የጎላ እንዲሆን በስልጠና ማብቃት እንደሚገባ ተናግረዋል። በክልሉ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ስልጠናው ይህን ችግር እንደሚቀርፍም አመላክተዋል። የሴቶች ጉዳይ በሁሉም ተቋማት ተካቶ እንዲሰራ በማድረግ የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን ማሳደግ እንደሚገባም ወ/ሮ ነጅሚያ ተናግረዋል። የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ወ/ሮ እናትአለም ሀብተማርያም ሴቶች ያላቸውን አቅም እንዴት ማውጣት እንደሚገባቸው ግንዛቤ ያገኘሁበት ስልጠና መሆኑን ገልፀው፣ በዚህ ረገድ የነበሩባቸውን የክህሎት ክፍተቶችን መቅረፍ የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል። ወ/ሮ በረከት ታደሰ ስልጠናው፣ ሴቶች ጠንካራ ሆነን በመስራት ውጤት ማምጣት እንድንችልና በራስ መተማመናችን እንዲጨምር አድርጓልም ብለዋል። ሌላኛዋ የስልጠናው ተሳታፊ ወ/ሮ አይናለም አበበ ሴቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እንዲጨመር፣ ውሳኔ ሰጪነታቸው እንዲጎለብትና ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችሉ ስልጠናው አጋዥ ስለመሆኑ ጠቁመዋል። መሠረታዊ የመሪነት ጥበብና ሴቶችን ማብቃት እንዲሁም በሥርዓተ ፆታ አካቶ ፅንሰ ሀሳብና መመሪያ ዙሪያ በተሰጠው ስልጠና ያገኙትን ግንዛቤ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ሰልጣኞቹ ገልፀዋል።