Skip to main content
news18

በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ የሆነች ሀገርን ለመገንባት የሴቶችን አቅም በሁሉም ዘርፍ ማጎልበት እንደሚገባ ተገለፀ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ከክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም ከክልሉ ሴቶች ክንፍ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የሴቶች አቅም ማጎልበቻ ስልጠና በሳጃ ከተማ እየተሰጠ ነው። የሴቶችና ህፃናትን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን እየሰራ ይገኛል። በዛሬው እለት መሰጠት የጀመረው የሴቶች አቅም ግንባታ ስልጠናም የዚሁ አካል ስለመሆኑ ተገልጿል። በስልጠናው ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብለቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለአመራርና ፈፃሚዎች የአጫጭር እንዲሁም የረጃጅም ግዜ ስልጠናዎችን መስጠትና በክልሉ ዋና ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ማካሄድ የአካዳሚው ዋና ተግባራት ስለመሆናቸው ገልፀዋል። ሴቶችን ያላከተተ የትኛውም ስራ ውጤታማ የማያደርግ በመሆኑ የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶችና ህፃናትን በሁሉም እንቅስቃሴዎች በተገቢው በማካተት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። እንደ ሀገር የተጀመሩ ተግባራትን በውጤታማነት ለማከናወን የሰው ሃብታችንን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም የተለያዩ ያደጉ ሀገራትን ተሞክሮ በምሳሌነት በማንሳት ለሚሰሩ ስራዎች ውጤታማነት የሰው ኃይልን በተለያየ ዘርፍ ብቁ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። የሴቶችን አቅም ለማጎልበት የተዘጋጀው ስልጠና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚተገበሩ ተግባራት በክህሎት በተደገፈ መልኩ እንዲፋጠን ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። ለሁለተኛ ዙር እየተሰጠ የሚገኝ ስልጠና መሆኑን የገለፁት አቶ ተስፋዬ ሰልጣኞች ስልጠናውን በጥሞና በመከታተል ገንቢ ክህሎት አዳብረው ማሄድ እንዳለባቸው አመላክተዋል። በስልጠናው ማስጀመሪያ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ዘቢባ መሀመድናስር እንዳሉት ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ የሴቶችና ህፃናትን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት በማለም የተዘጋጀ ስልጠና ሚናው ከፍተኛ ስለመሆኑም ኃላፊዋ ገልፀዋል። ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል በቀጣይ ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባቸው አሳስበዋል። በመሰረታዊ የመሪነት ጥበብ ሴቶችን ማብቃት፣ በስርዓተ ፆታ አካቶ እንዲሁም በስርዓተ ፆታ አካቶ ትግበራ መመሪያ ላይ ያተኮረ ስልጠና በተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ይሆናል።