Skip to main content
news17

ሴቶች ለሚያጋጥማቸው ማናቸውም ችግሮችና ጫናዎች እጅ ባለመስጠት የአመራርነት ሚናቸውን በጥራትና በብቃት መወጣት ይገባቸዋል- ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድናስር። የክልሉ የሴት አመራሮች የጋራ ፎረም የልምድ ልውውጥና የስልጠና መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል። በሴት አመራሮች ፎረሙ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬ የስራ ላይ ተሞክሮና ልምድ ለፎረሙ ተሳታፊ አመራሮች አካፍለዋል። ሴቶች የተሰጣቸውን የተኛውንም ኃላፊነት በብቃትና በውጤታማነት መወጣት እንደሚችሉ እስከሁን ያለፉበትን የስራ ተሞክሮ በማንሳት ሴቶች እድሉን ከገኙ ምንም መስራት እንደሚችሉ አብራርተዋል። የሴት አመራሮች ፎረምን በማጠናከር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋጋጥ እንደሚገባ የምክክር መድረኩን ያመሩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዘቢባ መሀመድናስር ገልፀዋል። የፎረሙ መጠናከር ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ሁሉም ሴቶች በተመደቡበት ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው አመላክተዋል። በአጠቃላይ የሴቶች ተሳትፎ፣ እኩል ተጠቃሚነትና የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማጠናከር እንደ ክልል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ወ/ሮ ዘቢባ አስረድተዋል። ሴቶች ለሚያጋጥማቸው ማናቸውም ችግሮችና ጫናዎች እጅ ባለመስጠት የአመራርነት ሚናቸውን በጥራትና በብቃት መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። በጥናት የተደገፈ የአመራር ውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማጎልበትና ውጤታማ የሆነ የመሪነት ተግባቦትን ለማዳበር የሚያግዝ ስልጠና በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ ረ/ፕሮፌሰር አንተነህ መሎ ለሴት ፎረም አመራሮች በመስጠት ገንቢ ውይይት ተደርጎበታል። በመጨረሻም የቀድሞው የፎረሙ አመራሮች በስራ አስፈላጊነት ወደ ሌሎች ተቋማት መሄዳቸውን ተከትሎ በምትካቸው የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድናስርን የፎረሙ ሰብሳቢ፣ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ይርዳውንና የክልሉ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ኃለፊ ዶክተር ፈለቀች ተ/ማሪያምን ምክትል ስብሰባዎች አድርጎ በመምረጥ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል።