Skip to main content
news16

የስርአተ ፃታ ጉዳይ የሴቶች ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን በመገንዘብ ፤ለሴቶች መብትና ደህንነት መጠበቅ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ልወጣ ይገባል- ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ። የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ከፍ በማድረግ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናችንን እንወጣ በሚል መርህ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ የሴት አመራሮች የጋራ ፎረም የምክክርና የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ ክልላዊ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። ከሀገራችን ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ቁጥር የያዙት ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፓለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት ከምንጊዜውም በተሻለ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በምክክር መድረኩ መክፈቻ የገለፁት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘቢባ መሀመድናስር ናቸው ። በቀጣይም በየደረጃው የሴት አመራሮችን አቅም ለማጎልበትና የአመራርነት ሰጪነት ሚናቸውን ይበልጥ ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል ። የመድረኩ ዋነኛ አላማም የበዙና የበቁ ሴት አመራሮችን ማፍራት እንደመሆኑ በዘርፉ እንደ ሀገር በ2025 ለመድረስ የተያዘውን ሽፋን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም በኃላፊነትና ባለቤትነት ስሜት መስራት እንዳለበት ወይዘሮ ዘቢባ ተናግረዋል። በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፋት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፅህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት ባለፉት 5 አመታት በልዩ ትኩረት ተሰርቷል ብለዋል። የስርዕተ ፆታ ጉዳይ የሴቶች ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን በተገቢው በመገንዘብ ለሴቶች መብትና ደህንነት መጠበቅ በባለቤትነት መስራት ይገባል ብለዋል። በመድረኩ በሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናታዊ ፁሑፍ በክልሉ የፓሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንሰቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር በዶክተር ፈለቀች ተክለማርያም እየቀረበ ነው።