
ኢትዮጵያ የህጻናት መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እያከናወነች ያለውን ተግባር ከፖሊሲው ጋር በማጣጣም ስኬታማ እንዲሆን በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ነች - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት ድርጅት (ኢ.ጋ.ድ) አባል ሀገራትና በህፃናት ጉዳይ ዙሪያ የሚሰሩ የቀጣናው ሚኒስትሮች በተዘጋጀው የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍ መግለጫ ላይ የስምምነት ፊርማቸውን አኑረዋል። በኢጋድ አባል ሀገራት በረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ሲካሄድ የነበረው የቴክኒክ ሙያተኞች ኮንፍረንስ በዛሬው ዕለት ተጠናቅቋል። በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ፊርማቸውን ያኖሩት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ በቀጣናው የሚኖሩ ህጻናት በድህነት፣ በጤና ተደራሽነት እጥረት፣ የግጭትና ስደት ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን በመግለጽ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መስጠትና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። በኢጋድ የተዘጋጀው የፖሊሲ ማዕቀፍም ህፃናትን በተመለከተ በኢትዮጵያም ሆነ በቀጣናው ያለውን የህፃናት ጥበቃና ማህበራዊ ልማት ስራዎች በተቀናጀ መልኩ ለማስቀጠል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ የህጻናት መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እያከናወነች ያለውን ተግባር ከፖሊሲው ጋር በማጣጣም ከአባል ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ክብርት ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል። የፖሊሲ ማዕቀፉ ላለፉት ሶስት ቀናት በአባል ሀገራት ኮሚሽነሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የህጻናት ባለሙያዎች፣ የውጭ ጉዳይ ተወካዮች፣ ህጻናት እና አጋር አካላት ሰፊ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል። በዛሬው ዕለትም ፖሊሲው ለቀጠናው ሃገራት የህጻናት መብት መከበር እና ጥበቃ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተገኙ ግብዓቶች ተካተው እንዲጸድቅ ስምምነት ተደርሷል፡፡ ዘገባው የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ነው