
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በጤናቸውና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሻሻል ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ማህበር ጽ/ቤት ለዞኖችና ለልዩ ወረዳ አመራሮች የማህበሩ ፋይናንሻል አሰራር ላይ፤ የማህፀን ጫፍ ካንሰር እና የጡት ጫፍ ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በወራቤ ከተማ ሰጥቷል። የማህፀን ጫፍ ካንሰር፣ የጡት ጫፍ ካንሰር እና የማህፀን ውልቃት ምንነትና ከመከላከያ ተግባራት ጋር በተያየዘ የክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህፃናት ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ወይንሸት እምሩ በቀረቡት ሰነድ ሰፊ የግንዛቤ ማብራሪያ ተሰጥተዋል። በሽታዎቹን ለመከላከል ሁሉም አካላት በተቀናጀ መልኩ መስራት ይገባቸዋልም ተብሏል። በሽታው በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች በፍጥነት ወደህክምና ተቋማት መሄድ እንደሚገባቸው ተገልጿል። የማህፀን ጫፍ ካንሰር ለመከላከል ከ2011 ጀምሮ ለሰባት አመታት እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 አመት ለሆናቸው ሴቶች ክትባቱ በየአመቱ እየተሰጠ እንደሆነም ተጠቁሟል። የክልሉ ሴቶች ማህበር አጠቃላይ የፋይናንሻል ተግባራትን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሰነድ በማህበሩ የኦዲት ቁጥጥር አመራር ኮሚቴ ወ/ሮ አስቴር ከበደ ለመድረኩ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል። በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ፎዚያ መሀመድ እንደገለፁት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል። እንደ ክልሉ የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ፕሬዚዳንቷ የክልሉ ሴቶች ማህበር ከ5 መቶ 52 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ገልጸዋል። የክልሉ ሴቶች ማህበር ሴቶች የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ከተለያዩ በሽታዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ ከተለያዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን እየተሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል። የሴቶች ጤናቸው እንዲሻሻልና የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲጎለብት የሁሉም አካላት ጥረት አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ አባልና የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር ይርዳው በበኩላቸው የሴቶችን ሁሉአቀፍ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሴቶች ማህበርን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል። የሴቶች ማህበር ጽ/ቤት የማህበሩን እንቅስቃሴ ለማጠናከርና የማህፀን ጫፍ ካንሰር፣ የጡት ጫፍ ካንሰር እና የማህፀን ውልቃት ምንነትና ከመከላከያ ሴቶች ጥሩ ግንዛቤ ኖሮኣቸው እራሳቸውን ከበሽታው እንዲጠብቁ የውይይቱ መዘጋጀት ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል። እናት የሀገር መሰረት በመሆኑዋ የሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ ሴቶችን አካተው መከናወን እንደሚገባቸው ጠቁመው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው እስከ ቀበሌ መውረድ እንደለበት ተናግረዋል።